EHPEA

ሆርቲፍሎራ ኤክስፖ 2026 (HortiFlora Expo 2026) በርካታ የውጪ ተሳታፊዎችን እየሳበ ይገኛል - EHPEA

ሆርቲፍሎራ ኤክስፖ 2026 (HortiFlora Expo 2026) በርካታ የውጪ ተሳታፊዎችን እየሳበ ይገኛል

ተጨባጭ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ በማድረግ እድገቱን በማስቀጠል ላይ የሚገኘውን የሀገራችንን ሆርቲካልቸር ዘርፍ በመመልከት የተለያዩ ዓለምአቀፍ የዘርፉ ተዋንያን በአዲስ አበባ በሚካሄደው በሆርቲፍሎራ ኤክስፖ 2026 (HortiFlora Expo 2026) ላይ ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡

“መጪው ጊዜ የሆርቲካልቸር ነው፡፡” በሚል መሪ ቃል ለ10ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር በአዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ሴንተር ከመጋቢት 15 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በሚካሄደው የግብርናው ንዑስ ዘርፍ ልዩ የንግድ ትርዒት ላይ ለመሳተፍ እስከ አሁን ድረስ ከ100 በላይ የኤግዚቢሽን አቅራቢዎች ተመዝግበዋል፡፡

የውጭ ሀገር የዘርፉ ተዋንያን በሁነቱ ላይ ለመሳተፍ የሚያሳዩት ፍላጎት በሀገራችን ማኅበረሰብንና አካባቢን በሚገባ ታሳቢ በማድረግ፤ በዘላቂ ልማት መርሆች የሚዘወረው የሆርቲካልቸር ዘርፍ ፈጣን እድገት በዓለምአቀፍ ደረጃ እውቅናን እያገኘ መምጣቱን የሚያመላክትና በዘርፉ ስኬታማነትና አዋጭነት ላይ ያላቻውን እምነት የሚያሳይ ነው፡፡

ይህም እውነታ ለበለጠ ውጤት እንዲሁም መጪውን ጊዜ በዘርፉ ስኬት ለማድመቅ ለአበባ አምራችና ላኪዎች ማኅበር እና ለሌሎች የሀገራችን ባለድርሻ አካላት ኃይል የሚሆን ግባት ነው፡፡

ማኅበሩ ከኤችፒፒ ወርልድዋይድ (HPP Worldwide,) ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው ሆርቲፍሎራ ኤክስፖ 2026 ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ማለትም ከአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከእስያ እና ከሰሜን አሜሪካ የሚመጡ አምራቾችን፣ ላኪዎችን፣ ገዥዎችን፣ ባለሀብቶችን፣ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎችን እና ፖሊሲ አውጪዎችን የሚያገናኝ ሁነኛ መድረክ ነው።

ከኤግዚቢሽን ባሻገር፣ ሁነቱ የንግድ ተቋማት እርስ በእርሳቸው እንዲሁም ከሸማቾችና ከመንግሥት ጋር ለሚያርጉት የአንድ ለአንድና የአቻ ለአቻ ውይይቶች አመቺ መድረክ ይፈጥራል፡፡

በተጨማሪም በፈጠራ፣ ዘላቂነት ባለው የልማት ሥራ፣ በሎጂስቲክስ፣ በፋይናንስ እና በዓለምአቀፍ ገበያ አዝማሚያዎች ላይ እንዲሁም በሚገባ አዋጭ የሆኑ የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎችን በመፍጠር ዙሪያ ላይ የሚያጠነጥኑ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ውይይቶች ይካሄዳሉ።

ከ150 በላይ ኤግዚቢሽን አቅራቢዎች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀው ሆርቲፍሎራ ኤክስፖ 2026 በአፍሪካ ሆርቲካልቸር እውን እየሆነ ከሚገኘው ደማቅ ስኬት ተቋዳሽ ለመሆን ለሚፈልግ ሁሉ ሊያመልጥ የማይገባው ልዩ አጋጣሚ ነው፡፡

የኤግዚቢሽን አቅራቢዎች ምዝገባ ክፍት ስለሆነ በዚህ ወሳኝ ዝግጀት ላይ ለመሳተፍ ይፍጠኑ!

https://www.hortifloraexpo.com

Contact Info

Location : Micky Leyland Avenue on the Road to Atlas Hotel, NB Business Center; 6th floor; Room #603
Phone : +251 11 6636750
P.O.Box: 22241 Code 1000
Email: info@ehpea.org

Join The Newsletter