EHPEA

ወርቃማው የሦስትዮሽ ትብብር ለውጤታማ የሆርቲካልቸር ልማት - EHPEA

ወርቃማው የሦስትዮሽ ትብብር ለውጤታማ የሆርቲካልቸር ልማት

በተፈጥሮ ሀብት የታደሉ እንዲሁም ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎችና መልካም አጋጣሚዎች የተፈጠረላቸው ሀገራት ግብርናቸውን በተለይ የሆርቲካልቸር ንዑስ ዘርፋቸውን በሚገባ አልምተው ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የተለያዩ ስልታዊ አካሄዶችን በመንደፍ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ይንቀሳቀሳሉ።

በዚህ ረገድ ዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂዎችን (Modern Technology) እና አዳዲስ ችግር ፈቺ ዘዴዎችን (Innovative Methods) በመጠቀም ግብአትን፥ ጉልበትንና ጊዜን በመቀነስ ከዘርፈ-ብዙ ጥቅሞች ጋር ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግና ተጠቃሚነትን ለማስፋት የሆርቲካልቸር ልማት ከሚሳለጥባቸው አካሄዶች አንዱ በቁርጠኝነት የሚተገበር የኢንዱስትሪ፥ የትምህርት/ምርምር ተቋማት እና የመንግስት የሦስትዮሽ ትብብር ነው።

በተለያዩ ሀገራት በተለይ በኔዘርላንድስ በስፋት በመተግበር ላይ የሚገኘውና የሀገራቱን የሆርቲካልቸር ልማት በአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች እና መጠነ ሰፊ ጥቅም ባለው የምርምር ውጤት በማሳለጥ፤ በትብብር ተሳታፊዎች ዘንድ ያሉ ሀብታትን (Resources) በአግባቡ በመጠቀም ከኢንዱሰትሪው የሚገኘውን የጋራ ተጠቃሚነትን በማላቅ፤ የሀገር ልማትንና ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት እንዲፋጠን ይህ ወርቃማ ሦስት ማዕዘናዊ የትብብር ሞዴል (Triple Helix model –Golden Triangle) እያበረከተ ያለው ድርሻ እጅግ ከፍተኛ ነው።

በቅርቡ የኢትዮጵያ አበባ፥ አትክልትና ፍራፍሬ (ሆርቲካልቸር) አምራች ላኪዎች ማኅበር እና የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት በትምህርት/ምርምር ማዕከላትና በኢንዱሰትሪው መካከል የሚደረግ ትብብርን በማጠናከር ረገድ እንዲሁም በተግባራዊነቱ ላይ ያተኮረ ውይይትና የመስክ ጉብኝት በሆለታ የፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ተካሂዷል።

በዝግጅቱም ላይ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመጡና ከኮሌጁ የተወጣጡ ተወካዮች እንዲሁም የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር፥ የማኅበሩ የስልጠና ማዕከል ባልደረቦችና በሆለታ የሚንቀሳቀሱ የማኅበሩ አባል እርሻዎች ተወካዯች ተሳትፈዋል።

የሦስትዮሽ ትብብር በኢንዱስትሪው አልሚዎች ዘንድ ያለውን ሀብታትን እና እሴቶችን በትምህርት/ምርምር/ልህቀት ማዕከላት ካሉ እውቀቶች፥ የምርምር ውጤቶችና ለሰርቶ ማሳያነት ከሚውሉ ሀብታት ጋር እንዲሁም ከመንግስት አጋዥፖሊሲዎች፥ አቅርቦቶችና ሌሎች ሀብቶች ጋር በስልት በማቀናጀት የሚተገበር አዋጭና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎላ የልማት አቀራረብ ነው።

እጅግ በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችና አሰራሮች ከሌሎች ሀብቶች ጋር የሚንቀሳቀሱ የኢንዱስትሪው አልሚዎች ከትምህርት/ምርምር/ልህቀት ማዕከላት የሚፈልጓቸውን የሰለጠነ የሰው ሃይል፥ ለተሻሻሉ አሰራሮች የሚረዱ የምርምር ውጤቶችንና ሌሎች ሀብታትን በመውሰድና በምትኩ ለተማሪዎች የተግባር ላይ ስልጠና በራቸውን ክፍት በማድረግ፥ የሰለጠነ የሰው ሃይል ከተቋማቱ በመውሰድ የስራ እድልን በመፍጠር፥ እንዲሁም ከተቋማቱ ጋር በልዩ አጋርነት አስፈላጊውን ሀብት በመጋራትና በጋራ ሀብትን በተመረጡ ልማቶች ላይ በማዋል አስቻይ በሆኑ በመንግስት ፖሊሲዎችና በሌሎች ጥቅማጥቅሞችና ድጋፍ በመታገዝ ትብብሩን ይተገብራሉ።

ይህ በተለያዩ ሀገራት ላይ በመተግበር ያለና ውጤታማነቱ የተመሰከረለት የትብብር አካሄድ በኢትዮጵያ እንዲስፋፋና የሀገሪቱን እምቅ አቅም በሚገባ ለመጠቀምና ከሆርቲካልቸር የሚገኘውን ዘርፈ-ብዙ ጥቅም በእጅጉ ለማሳደግ እንደሚረዳ የኢትዮጵያ አበባ፥ አትክልትና ፍራፍሬ (ሆርቲካልቸር) አምራች ላኪዎች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ አበክረው ይናገራሉ።

በቅርቡ በሆለታ የፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በተዘጋጀው ውይይት ላይ ሲናገሩ ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን አስቻይ የሆነ የሦስትዮሽ ትብብር በኢትዮጵያ በስፋት ተግባራዊ በማድረግ እጅግ አርዓያነት ያለው ሥራ መሥራት ይቻላል ብለዋል።

ኢንዱስትሪ፥ የትምህርት/ምርምር/ልህቀት ተቋማት እና መንግሥት በቁርጠኝነት የሚሳተፉበትን ይህንን ትብብር በሚገባ ተግባራዊ ለማድረግና ለማጠናከር እንዲሁም ለችግሮች የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ የሚረዱ የሕግና የአሰራር ማዕቀፎች ለትብብሩ ተግባራዊነትና ውጤታማነት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው በመግለጥ አቶ ቴዎድሮስ ለዚህም ተግባር የቁልፍ ባለድርሻ አካላትን ያላሰለሰ ጥረት ጠይቀዋል።

እነዚህን ሦስት ሁነኛ ተዋንያን በማቀራረብ፤ ሀብትን፥ ፖሊሲን፥ መዋለ ንዋይንና እውቀትን አስቻይ በሆነ አሠራር በማቀናጀት ተግባራዊነትን ማረጋገጥ የጋራ ተቃሚነትን የሚያሰፋ ትርጉም ያለው ውጤት ከማስገኘት ባለፈ በሀገርና በአህጉር ደረጃም አርዓያነትን ያጎላል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

ተስማሚና አመቺ በሆነ የተፈጥሮ ሀብት ከመታደል በተጨማሪ፤ እጅግ በተሻሻለ የግብርና አሠራር የመጠቁ ዘመናዊ የሆርቲካልቸር እርሻዎች በሀገራችን መበራከታቸው፤ በቂና ምቹ ቦታ፥ ከመሠረተ ልማትና ሌሎች በጣም አስፈላጊ ከሆኑ አገልግሎቶች (facilities) ጋር በማስተባበር የላቀ የእውቀት፥ የክህሎትና የልምድ ክምችት ያለባቸው የትምህርት፥ የምርምር፥ የልህቀት ተቋማት እንዲሁም አስተዋጽኦቸው ጉልህ የሆነ እጅግ የካበተ እውቀትና ልምድ ያላቸው በርካታ የዘርፍ ባለሙያዎች መኖራቸው፤ በመንግሥት አጋዥ ፓሊሲና ሌሎች አስቻይ ድጋፎች መቅረባቸው፤ ለሦስትዮሽ ትብብሩ ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥር ይህንን አስቻይና ውጤታማ የሚያደርግ ትብብር ማጠናከር፥ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ይንቀሳቀሱ ዘንድ ለባለድርሻ አካላቱ አቶ ቴዎድሮስ ጥሪ አቅርበዋል።

ለዚህም የተጀመሩ ሥራዎችን ማቀጣጠል፤ ተቀራርቦ በመወያየት፥ አስቻይ የሆነ የአሠራርና የሕግ ማዕቀፍ በጋራ ቀርጾ፤ ምቹ መድረክ በመፍጠር ተግባራዊነቱ ላይ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

ፍሬያማ በሆነ ውይይትና በጥሩ የመስክ ጉብኝት ታጅቦ የተከናወነው ዝግጅት በሆለታ የፖሊቴክኒክና በኢንዱሰትሪው መካከል ለሚደረግ ፋይዳው የላቀ ትብብር ሁኔታዎችን የሚያመቻች ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ አቋቁሞ፤ እርሻዎችም ከኮሌጁ ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጠው ዝግጅቱ በስኬት ተጠናቋል።

Contact Info

Location : Micky Leyland Avenue on the Road to Atlas Hotel, NB Business Center; 6th floor; Room #603
Phone : +251 11 6636750
P.O.Box: 22241 Code 1000
Email: info@ehpea.org

Join The Newsletter