ዘመንን በዘመናዊነት ፤ አዲስ ዓመት ብቷል - አበባው ያብባል ፥ አዝመራው ዓመቱን ሙሉ ይጎመራል - EHPEA

ዘመንን በዘመናዊነት ፤ አዲስ ዓመት ብቷል – አበባው ያብባል ፥ አዝመራው ዓመቱን ሙሉ ይጎመራል

በኢትዮጵያ አዲሱ ዘመን አንድ ብሎ የሚጀምረው በውጪዎቹ ዘጠነኛው ወር በሆነው በሴፕቴምበር በሀገርኛው መስከረም ሲሆን፤ ይህ ወቅት ክረምቱ እየተጠናቀቀ፤ ዝናቡ እንዲሁም የወንዙ ጅረት ሙላቱ እየቀነሰ፤ ፀሓይ ስትደምቅ ምድሪቱ ጠፈፍ እያለች እየደረቀች የምትታይበት ወቅት ነው።

በዚህ ወር ምድሪቱ ለምልማ፥ በወቅታዊው አበባ አጊጣ፥ ጋራው ሸንተረሩ ለምልሞ ተሸልሞ ይታያል። በሁለትና በሦስት ወራት እድሜ ውስጥ የተፈጥሮው ውበት ይደበዝዛል፤ ይረግፋል። ምናልባት በመሀል ሰማዩ በተወሰነ ደረጃ ከብዶ ምድሪቱ ጠል ካገኘች ካልሆነ በቀር፤ ዞሮ ወቅቱ እስኪመጣ ይህ ወቅታዊ አበባ፥ የተፈጥሮ ልምላሜ፥ የፈካው ውበት አይገኝም።

በዘመናዊው ሆርቲካልቸር ንዑስ ዘርፍ ነገሩ የተለየ ነው። በዘመናዊው ግብርና የአበባ፥ አትክልትና ፍራፍሬ (ሆርቲካልቸር) ልማት ዓመቱን ሙሉ አበባው ያብባል፤ የአትክልት የፍራፍሬ ሰብል አዝመራው ይጎመራል፤ ምርቱ ይሰበሰባል። የጥረት፥ የትጋት፥ የድካም ዋጋ በሚገባ ይከፈላል።

እኮ በምን ምክንያት ዓመቱን ሙሉ?            

ከግማሽ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ አንድ ክፍለ ዘመንና ከዚያም በላይ በሚቆጠር ደረጃ የግብርናውን ንዑስ ዘርፍ በተደራጀ መልኩ እየተገበሩ ከሚገኙ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር በኢትዮጵያ ዘመናዊው የሆርቲካልቸር ልማት በጣም ልጅ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በተነጻጻሪ በአነስተኛ የመሬት ሽፋን ላይ እየተካሄደ ያለው ዘመናዊ የሆርቲካልቸር ልማት ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በውጤቱም በግብርናው ዘርፍ ከቡና ቀጥሎ ትልቁ የውጭ ምንዛሪ አስገኚ መስክ ለመሆን በቅቷል።

የከርሰ ምድር ውሃን በማልማትና ከብክለት ነጻ በሆነ መንገድ በማከማቸት፥ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የጠብታ (Drip Irrigation) እና የተመጠነ በቀጥታ ለተክሉ የሚደርስ መስኖን እንዲሁም ማዳበሪያን (precise irrigation & fertigation) በመጠቀም የተፈጥሮ ሀብትን እንዲሁም ግብአትን ቆጣቢ በሆነ አሠራር የሚተገበረው ዘመናዊው ሆርቲካልቸር ከግማሽ ቢሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር በማስገባት፥ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች በተለይ በገጠራማ አካባቢ ለሚገኙ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ እድል በመፍጠር እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ ለተሻለ አሠራርና ምርታማነት ፋይዳው የጎላ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል።

በሽታን እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን የሚቋቋሙ፥ ምርታማነትን በእጅጉ የሚያሳድጉ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የተሻሻሉ የሆርቲካልቸር ሰብል ዝርያዎችን፤ በጣም ዘመናዊ በሆነ ቴክኖሎጂ የተመጠነ መስኖንና ግብአትን በመጠቀም የሚተገበረው ግብርና አረንጓዴዎቹን አብያተ-ዕፅዋት (Green Houses) ዓመቱን ሙሉ በልምላሜ ያደምቃቸዋል።  

እነዚህ ዓመቱን ሙሉ በልምላሜ የሚደምቁት ዘመናዊ አብያተ-ዕፅዋት (Green Houses) በኢትዮጵያ የአበባ፥ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማኅበር ሥር በተሰባሰቡ አባላት በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በክምችት በሚገኙ (clustered) ሰፋፊ የንግድ እርሻዎች ላይ ተንጣለው ይገኛሉ።  

አዳዲስ ዘመናትን በዘመናዊነት

በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ንዑስ ዘርፍ በማኅበሩ ስልታዊ ሚናዎች፥ በአባላቱ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት፥ በዓለምአቀፍ ገበያ ፍላጎትና የጥራት መስፈርቶች አዎንታዊ ግፊት እንዲሁም በመንግሥስት ልዩ ትኩረትና ድጋፍ በፈጣን ዕድገት ላይ የሚገኝ ሲሆን አካባቢያዊና ማኅበራዊ ኃላፊነትን በሚገባ በመወጣት ዘመናዊ እርሻን በተሻሻለ አሠራርና በላቀ ቴክኖሎጂ በማቀላጠፍ ላይ ይገኛል።

ንዑስ ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሠራሩን በማዘመን፥ አካባቢን በሚገባ በመጠበቅና በመንከባከብ፤ የሥራ ላይ ደህንነትና የሠራተኞችን ጤና በማስጠበቅ እጅግ ከፍተኛ ጥራትና ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በማምረት ላይ ይገኛል።

በሀገሪቱ የሆርቲካልቸር ንዑስ ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተመዘገ ውጤት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከኬንያ ቀጥሎ አበባን በጥራትና በብዛት በማምረት ሁለተኝ ስትሆን በዓለም ደግሞ የአምስተኝነትን ቦታ ይዛ ትገኛለች። በአበባ የተመዘገበውን ስኬት በአትክልትና ፍራፍሬ ኢነዱስትሪዎች ለመድገም ብሎም የበለጠ ውጤት ለማምጣት በተጀመሩና ተጠናክረው በቀጠሉ ሥራዎች ጉልበት የሚሆኑ የሚያበረታቱ ፍሬዎች እየተገኙ ነው። ለዚህም ከሌሎች እትክልትና ፍራፍሬ መካከል በብዛትና በጥራት እየተመረቱ ያሉት የሙዝ፥ የአቮካዶና የስትሮበሪ ምርቶች ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው።

መልካም የግብርና አተገባበርን (Good Agriculture Practice) በሚገባ በመከተል ዘመናዊ እርሻን የሚያካሂዱት የማኅበሩ አባላት ዘመናዊ አሠራራቸውን ከሚያሳዩባቸው መንገዶች መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የሚገኘው የተቀናጀ የተባይ ቁጥጥር (Integrated Pest Management) አንዱ መገለጫ ነው። በዚህም በሰው-ሠራሽ የተባይ ቁጥጥር ላይ የሚደረግ ጥገኝነትን በመቀነስ ሕይወት ያላቸውን ኃይሎች (Biological Agents) መጠቀምና ሁለቱን በማቀናጀት ዘመናዊ እርሻዎቹ ሰብሎቻቸውን ይከላከላሉ። በዚህም በተቀናጀ የተባይ ቁጥጥር እርሻዎች የሠራተኞችንና የአካባቢ ደህንነት ይጠብቃሉ፤ ለዓለምአቀፍ ደረጃ የሚቀርቡ እጅግ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ደረጃቸውን ያስጠብቃሉ፤ ጥብቅ የዓለምአቀፍ ገበያ የጥራት መስፈርቶችን በሚገባ ያሟላሉ። በዚህ ረገድ ከውጪ ገቢ የሚያደርገውን ምርት ለማስቀረት የራሱን የተፈጥሮ ተባይ መቆጣጠሪያ ለማምረት የሚያችለውን ዘመናዊ ማዘጋጃ ቤት (mass rearing facility) አቋቁሞ በተጠናቀቀው ዓመት ምርቱን የጀመረ እርሻ እንዳለ ልብ ይሏል። ይህም ጅማሮ በሌሎች እርሻዎች እንደሚስፋፋ ይጠበቃል።

ኮምፖስትና ለመስክ ሥራ የሚያገለግሉ አንዳንድ ግብአቶችን በቀላሉ በዚያው በእርሻ አካባቢ በማዘጋጀት፤ ተረፈ ምርትን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ውጋጅን በመቀነስና ወደ ሀብት በመቀየር (from waste to value) የአካባቢንና የኅብረተሰብን ደህንነት በጠበቀ መልኩ እርሻን ኃላፊነት በተሞላው መንገድ ማከናወን እንዲሁም ዘመኑን የዋጀ ግብርናን ማሳደድ፥ በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥብቅ እየሆነ የመጣውን በዓለምአቀፍ ደረጃ አዋጭ ከሆኑ ገበያዎች የሚወጣ የጥራት መስፈርትን እግር በእግር እየተከተሉ አሠራርን ማዘመን፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁመናን ማሻሻል፤ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሀብት – ገንዘብ፥ ጉልበት፥ ጊዜ፥ እውቀት የፈሰሰበትን ሥራ መና እንዳይቀር ይታደጋልና ይዋል ይደር የማይባል ጉዳይ ነው። ስለሆነም በአባላቱ ተነሳሽነት፥ በማኅበሩ የቁርጠኝነት ጥረት፥ በልማት አጋሮች ትብብርና በመንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ የሀገሪቱ ሆርቲካልቸር ዘርፍ በተለይ በሰፋፊ እርሻዎች የሚካሄደውን ግብርና የማዘመን ሥራ እንደቀጠለ፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገም ይገኛል።

ከውጭ ምንዛሪ፥ ከሥራ እድል ባለፈ ያሉ ሰናይ ተግባራት – በተለይ በአዲስ ዓመት

ዘመናዊ፥ ሰፋፊ የሆርቲካልቸር የንግድ እርሻዎች (Commercial Farms) አነስተኛ አርሶአደሮችን ባሳተፈና በደገፈ መልኩ እንዲሁም የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ሲንቀሳቀሱ በርካታ የማኅበራዊ ኃላፊነት ተግባራትን ያከናውናሉ።

ለአካባቢው ነዋሪዎች በተለይ ለወጣቶችና ሴቶች የሥራ እድልን ከመፍጠር ባሻገር የሆርቲካልቸር እርሻዎች በሚንቀሳቀሱበት አካባቢዎች ከዚያም ባለፉ ቦታዎች ትምህርት ቤቶችንና የሕክምና ተቋማትን ይገነባሉ፥ በቁሳቁስ ይደግፋሉ፥ በእድሳት እገዛ ያደርጋሉ። ለዚህም በባቱ (ዝዋይ)፥ በቆቃ፥ በዝቋላ፥ በሰበታ በሌሎችም ክላስተሮች የሚገኙ እርሻዎች የተከናወኑ ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው። በበርካታ እርሻዎች የንጹህ ውሃ አቅርቦት፥ የንጽህናና የመጸዳጃ ቤት ፕሮጀክቶች የተከናወኑ ሲሆን በሆለታ፥ ዝቋላና በሌሎች አንዳንድ እርሻዎች ደግሞ ሕዝብን በከፍተኛ ደረጃ የሚያገለግሉ ማገናኛ መንገዶች ተሠርተዋል።

ትምህርት ቤቶችን ከማሰራት፥ ከማሳደስና ቁሳቁሶችን ከማሟላት በተጨማሪ ይህ ወቅት የአዲሱ ዘመን ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ ነውና በርካታ እርሻዎች በአካባቢያቸው ለሚገኙ የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ይለግሳሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች እርሻዎች የአቅመ ደካሞችን ቤቶች አሠርተዋል፥ ለአንዳንዶችም የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ። እንደ ዝቋላ ያሉ እርሻዎች የአረጋውያንንና የአካል ጉዳተኞችን ተቋማት ይረዳሉ።

በዘመናዊ የሆርቲካልቸር ልማት ምንጩን መንከባከብ

የአካባቢንና የማኅበረሰብን ደህንነት በመጠበቅ፥ በማልማትና በመንከባከብ ኃላፊነትን በሚገባ በመወጣት በንግድ እርሻዎች የሚተገበረው የሆርቲካልቸር ልማት ሠራተኞቹን፥ ምንጩን በመንከባከብ ረገድ የሚያከናውነውና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣው ሥራ በጣም የሚያስመሰግን ነው። የሥራ ላይ ደህንነትን መጠበቅ፥ የሠራተኞችን ጤና መንከባከብና አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትንና ክፍሎችን በማሟላት ምቹ የሥራ ቦታ መፍጠር የእርሻዎቹ ልዩ ትኩረቶች ናቸው። በሥራ ቦታ በነጻ እንዲሁም በከፍተኛ ድጎማ የሚከናወን ምገባና የጤና ክብካቤ አገልግሎት በሆርቲካልቸር እርሻዎች የሚሰጥ በምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ተግባር ነው። ለሠራተኞች በተለይ ለሴት ሠራተኞች ምቹ የሥራ ከባቢና ሁኔታ ለመፍጠር በሚደረጉ ክንውኖች የንጽህና መጠበቂያ፥ የልብስ መቀየሪያና የእረፍት መውሰጃ ክፍሎችና ቦታዎች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በበርካታ እርሻዎች መገንባታቸው ለምንጩ ክብካቤ የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው። በአንዳንድ እርሻዎች በሚከናወነው የምግብና የሕፃናት ማቆያዎች የመሳሰሉት ልዩ ድጋፎች ወላድ ሠራተኞችን በእጅጉ እየረዱ ይገኛሉ። 

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሆርቲካልቸር ልማት፥ በሰፋፊ የንግድ እርሻዎች በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል የተፈጠረ ሲሆን ከእነዚህም 80 በመቶው ሴት ሠራተኞች ናቸው። በዚህም ረገድ ንዑስ ዘርፉን በዘላቂነት ለማሳለጥ ለእነዚህ ሴት ሠራተⶉች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፥ ፆታን መሠረት ያደረጉ ችግሮችን በሚገባ ለመከላከል እንዲሁም ሴት ሠራተኞችን በአመራር ቦታዎች ለማስቀመጥ በማኅበሩ ቁልፍ ሚና ተጫዋችነት በአባላቱም ተነሳሽነት የተለያዩ ስልታዊ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። የስነ-ተዋልዶና የአጠቃላይ ጤና አጠባበቅ፥ የስነ-ምግብ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሙያዊ ስልጠናዎች በተጠናከረ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። ፆታዊ ጉዳዮችን በሚገባ ለመቃኘትና ተገቢውን እንቅስቃሴ በተደራጀ መልኩ ለማድረግ በማኅበሩ የፆታ ክፍል (Gender Department) መሪና አስተባባሪነት በእርሻዎች ደረጃ የፆታ ኮሚቴዎች (Gender Committees) ተቋቁመዋል። በዚህም ምክንያት እጅግ አመርቂ ውጤቶች ተገኝተዋል።

ማኅበሩ በቁርጠኝነት የሚጫወታቸው ሚናዎች

ለሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንትና ቢዝነስ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር፤ ስነ ምህዳሩን ለመንከባከብና ለማሻሻል ማኅበሩ ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ የሀገሪቱ ንዑስ ዘርፍ ችግርን በመቋቋም በዘላቂነት እንዲለማ፥ ከንዑስ ዘርፉ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅም በእጅጉ እንዲያድግ እንዲሁም በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን በርካታ ስልታዊ ሥራዎችን ያከናወናል። አባላት የዓለምአቀፍ መልካም የግብርና አተገባበርን (Global Good Agricultural Practices – GlobalG.A.P.) በመከተል እንዲተጉ፥ አዋጭ የሆኑ ዓለምአቀፍ ገበያዎች የሚያወጧቸውን የጥራት መስፈርቶች በማሟላት ምርታቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አሠራሮችን እንዲተገብሩና ለዘርፉ ስጋት የሚሆኑ የፀረ-ሰብል ችግሮችን እንዲቋቋሙና እንዲቀርፉ ማኅበሩ የተለያዩ የአቅም ግንባታ መርሃግብሮችን በማከናወን ሥልጠናዎችን ለአባላቱ በመስጠት በእጅጉ ይደግፋቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በዓለምአቀፍ ገበያዎች ምርታቸውን በማስተዋወቅ እንዲሁም የገበያ ትስስሮችን በመፍጠር ሚናውን በቁርጠኝነት በመጫወት ላይ ይገኛል።

ንዑስ ዘርፉን በተመለከተ ከሚጫወተው ሚና በተጨማሪ ማኅበሩ የተለያዩ ማኅነራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በንቃት ይሳተፋል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶአደር እና የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የሚከናወኑ የከተማ ግብርና (Urban Agriculture)  እና የሽቅብታ እርሻ (Vertical Farming) ሥራዎችን በመደገፍ፤ በአነስተኛ ቦታ እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለቸውን የሆርቲካልቸር ምርቶች ለማምረት የሚያስችል ቴክኖሎጂና አሠራር እንዲስፋፋ፥ በከተማዋ የምግብ ዋስትናንና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፥ ለወጣቶችና ሴቶች የገቢ ማስገኛ ምንጮችን በመፍጠር የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በሚገባ እየተሳተፈ ይገኛል። ለዚህም ከሁለት የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ከ11 ክፍለ ከተሞች ለተወጣጡ ወጣቶችና ሴቶች በተግባር የተደገፈ ሥልጠናዎችን በመስጠት፤ የተጀመረው ልማት ይፋጠን ዘንድና እየተመዘገበ ያለውም ውጤት እንዲልቅ ማኅበሩ አስፈላጊ የሆኑ የግብርና ማከናወኛ ቁሳቁሶችን በቅርቡ ለግሷል። 

ማኅበሩ የአባላቱን ስኬታማነት የሀገሪቱን የሆርቲካልቸር ንዑስ ዘርፍ በእጅጉ ለማሳደግ በቁርጠኝነት የሚያደርገውን እንቅስቃሴና ጥረት በተጀመረው አዲስ ዓመት አጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ለዚህም ከግብርና ሚኒስቴር፥ ከግብርና ባለስልጣንና ከሌሎች የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም ከልማት አጋር ድርጅቶችና ዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ይሠራል።

ሆርቲፍሎራ – ዓመታዊው ዓለምአቀፍ የሆርቲካልቸር የንግድ ትርዒት

የሀገሪቱን የሆርቲካልቸር እምቅ አቅም ለተቀረው ዓለም ለማሳየት፥ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ፥ ለአባላቱ የገበያ ትስስርን ለመፍጠር፥ በአጠቃላይ ዘርፉን ለማዘመንና ለማሳደግ ማኅበሩ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ የተለያዩ ሁነቶች ወይም መድረኮች ላይ መሳተፍና በሀገር ውስጥ ሁነቶችን ማዘጋጀት ሲሆን ለዚህም ከዚህ በፊት በሁለት ዓመታት አንዴ ይካሄድ የነበረውና አሁን በየዓመቱ የሚካሄደው ሆርቲፍሎራ ታላቁና ዋነኛው ዝግጅት ነው።

ሆርቲፍሎራ ኤክስፖ የሆርቲካልቸር ንዑስ ዘርፍ ባለሀብቶችን፥ አምራቾችን፥ ላኪዎችን፥ ገዢዎችን፥ አግባብነት ያላቸውን የመንግሥት ተቋማትን፥ ቴክኖሎጂና ግብአት አቅራቢዎችን፥ ምርጥ ዘር አባዢዎችን፥ ኢንዱስትሪ መሪዎችንና ባለሙያዎችን፥ የትምህርትና የምርምር ተቋማትንና ሌሎችንም በእሴት ሰንሰለት ተሳታፊ አካላትን በአንድ ጣሪያ በማሰባሰብ ለሦስት ቀናት የሚካሄድ ታላቅ ዝግጅት ነው። ለዚህም ማኅበሩ ከኤችፒፒ ከተሰኘ ዓለምአቀፍ ተቋም ጋር በመተባበር በመዲናዋ አዲስ አበባ በየዓመቱ ያዘጋጀዋል። የ2019 ሆርቲፍሎራ ኤክስፖ (HortiFlora Expo 2027) በመጋቢት ወር በአዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የሚካሄድ ሲሆን ለዚህም ዝግጅቱ ከወዲሁ ተጀምሯል።

የመንግሥት ልዩ ትኩረትና ድጋፍ

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመነ እያደገ የመጣው የሆርቲካልቸር ንዑስ-ዘርፍ በመንግሥት ልዩ ትኩረትና ድጋፍ የዕድገቱን ዘላቂነት በሚያረጋግጥ ሀዲድ ላይ ይገኛል። መንግሥት ንዑስ-ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማለትም- የግብር እፎይታ፥ ከቀረጥ ነጻ ግብአቶች፥ የብድር ማመቻቸት፥ የመሬት አቅርቦትና ሌሎች ድጋፎችን ከማድረግ ባሻገር በተለያዩ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎችን በመቅረጽና ወደ ተግባር በማስገባት ሆርቲካልቸሩን እየደገፈ ይገኛል። ለዚህም ከአንድ ዓመት በፊት በግብርና ሚኒስቴር ይፋ ሆነው ወደ ሥራ የተገባባቸው የ10 ዓመት ብሔራዊ ሆርቲካልቸር ስትራቴጂና የ15 ዓመት የአቮካዶ ልማት ምርሃግብር ተጠቃሽ ናቸው።  ከዚህም በተጨማሪ ለአዳዲስ ባለሀብቶችና ለነባር እርሻዎች ማስፋፊያ የሚሆን መሬት አቅርቦትም እየተከናወነ ይገኛል።

አዲስ ዓመት ተጀምሯል – ትጋቱ ይቀጥላል። አበባው ዓመቱን ሙሉ ያብባል፤ አዝመራው ይጎመራል።

Contact Info

Location : Mickey Leland St,  on the Road to Atlas Hotel, NB Business Center; 6th floor; Room #603
Phone : +251 11 6636750
P.O.Box: 22241 Code 1000
Email: info@ehpea.org

Join The Newsletter