በዓለም እጅግ ተወዳጁ ፍሬ
ሀብሀብን እና አፕልን በሁለተኝነትና ሦስተኝነት ደረጃ አስከትሎ ሙዝ በዓለማችን እጅግ ከፍተኛ በሆነ መጠን በፍጆታነት የሚውል የፍራፍሬ ዓይነት ነው። በዚህም የተነሳ ሙዝ በዓለም እጅግ ተወዳጁ ፍሬ (World’s Favorite Fruit) በመባል ይታወቃል።
በተስማሚ ቦታና የአየር ንብረት በተለይ በኢንዱስትሪው በመጠቁ ሀገራት ዓመቱን ሙሉ በብዛትና በጥራት ሊመረት በመቻሉ፤ ለሰውነትና ለጤና በሚጠቅሙ ንጥረ ነገሮች የዳበረና ዋጋውም ተመጣጣኝ በመሆኑ ሙዝን በዓለም ለምግብ ፍጆታነት ከሚውሉ ፍራፍሬዎች የቀዳሚነትን ስፍራ እንዲይዝ አስችሎታል። ተአማኒ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓለማችን የሙዝ ምርት ፍጆታ 130 ሚሊዮን ቶንን ዘሏል።
ዓለም አቀፍ የሙዝ ምርትና ንግድ
ሙዝን እጅግ ከፍተኛ በሆነ መጠን የምታመርተው የዓለም ቀዳሚ ሀገር ሕንድ በዓመት ከ31 እስከ 35 ሚሊዮን ቶን የሚደርስ ምርት በማምረት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ታውለዋለች። በምርቱ በሁለተኝነት ደረጃ የምትቀመጠው እስያዊዋ ሀገር ቻይና በዓመት እስከ 12 ሚሊዮን ቶን የሚደርሰውን የሙዝ ምርቷን ልክ እንደ ሕንድ በሀገር ውስጥ ታስቀረዋለች።
የአህጉራችንን ሀገር ናይጄሪያን ጨምሮ ሌሎች እንደነ ኤንዶኔዥያና ብራዚል ያሉ ሀገራትም እያንዳንዳቸው ከ7 እስከ 10 ሚሊዮን ቶን በሚደርስ የምርት መጠን በሙዝ የዓለም ካርታ ላይ ደምቀው ይገኛሉ።
ከላይ የተጠቀሱት ግዙፍ የሙዝ አምራቾች በአንድ ጎራ ሳሉ ከዚህ ተወዳጅ ፍሬ የወጪ ንግድ ከፍተኛ የሆነ የውጪ ረብጣ የሚሰበስቡት ሀገራት በሌላ ጎራ በብዛት በላቲን አሜሪካና በካሪቢያን ተሰባስበው ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ ኤኳዶር፥ ኮስታሪካ፥ ሆንዱራስ፥ ጓቲማላ እና ኮሎምቢያ ተጠቃሽ ሲሆኑ በሌላ በኩል ፊሊጲስ በደቡብ-ምሥራቅ እስያ ፈንጠር ብላ ከጎራው ትሰለፋለች። ከእነዚህም መካከል በሙዝ ወጪ ንግድ ቀዳሚ ሀገር ኤኳዶር በዓመት 6̇.8 ሚሊዮን ቶን ምርት ወደ ውጪ በመላክ ከ 3.5 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር ገቢ ታደርጋለች።
እንደ ኮሎምቢያና ጓቲማላ ያሉ የዚሁ አካባቢ ሀገራት ከዓለምአቀፍ የሙዝ ምርት ንግድ በቢሊዮን የሚቆጠር የውጪ ምንዛሪን ገቢ ያደርጋሉ።
ለዓለምአቀፍ ገበያ የሚቀርበው የሙዝ መጠን ከ22 ሚሊዮን ቶን በላይ ሲሆን፤ በዚህ የዓለም ገበያ በብዛት የሚነገደው የሙዝ ዝርያ ወይም ዓይነት ደግሞ ካቬንዲሽ (Cavendish) የሚባለው ምርት ነው። በስፋት በኢትዮጵያ የሚመረተው ይህ ዝርያ መሆኑን ልብ ይሏል።
ከሙዝ ወጪ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ የመሆን አካሄድ
ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሙዝ ወደ ውጪ በመላክ ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሪ የሚያገኙ የላቲን አሜሪካ ሀገራት እንዴት ከዚህ ተወዳጅ ፍሬ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ሊሆኑ ቻሉ? ምን ምን መልካም አጋጣሚዎችና አስቻይ ሁኔታዎች አሏቸው? በምርቱ ወደ ላቀ ስኬት ለመድረስ ትኩረታቸውን በምን በምን ጉዳዮች ላይ አድርገው ሠሩ? እየሠሩ ይገኛሉ? የመሳሰሉት ጥያቄዎች በሙዝ እሴት ከፍተኛ እምቅ አቅም ያላቸውና ተጠቃሚነታቸውን በእጅጉ ማላቅ የሚችሉ ሀገራት ሊጠይቋቸው የሚገቡ፤ ስኬታማ ተሞክሮን ለመውሰድ የሚያስችሉ መልሶችን የሚያገኙባቸው ጥያቄዎች ናቸው።
ለሰብሉ ተስማሚ የሆኑ ሞቃታማ የአየር ንብረት፥ አፈር፥ ውሃ፥ የሰው ኃይል ወጪን ጨምሮ አዋጭ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፥ ለዘመነ የግብርና አሠራርና ቴክኖሎጂ የሚውል መዋለ-ንዋይ (ገንዘብ)፥ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፥ የምርቱን ወጪ ንግድ የሚያሳልጡ ሎጂስቲክስ፥ ትራንስፖርት፥ ዓለምአቀፍ ደረጃዎችን በተለይ አዋጭ የሆኑ የገበያ መዳረሻዎች የጥራት መስፈርቶችን ማሟላት፥ ኢንዱስትሪውን በሳይንሳዊ መንገድ ለማልማት የሚያስችል ጠንከር ያለ የምርምር ሥርዓት፥ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለማውጣት የሚያስችል የምርምርና የማዘጋጃ ቴክኖሎጂ/ቤተ-ሙከራ (Tissue Culture Technology)፥ ከገዢዎች ጋር የሚፈጠር መልካምና ጠንካራ የንግድ ስምምነትና ግንኙነት እንዲሁም አመቺ የሆነ የኢንቨስተመንትና የንግድ ሥርዓት መኖር እነዚህ ሀገራትን በሙዝ ኢንዱሰትሪ ለበርካታ ዜጎች ሥራን እንዲፈጥሩና ከምርቱ ወጪ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችለዋቸዋል።
የማኅበሩ አመላካች የሆነ ስልታዊ ጅማሮ
ኢትዮጵያ ጥራት ያለውን ሙዝ በከፍተኛ መጠን ለማምረት በሚያስችሉ የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች ሀገር ናት። ከዚህም በተጨማሪ እጅግ በዘመነ አሠራርና ቴክኖሎጂ ምርቱን በጥራትና በብዛት በማምረት ላይ የተሰማሩ እንደ ፍሪኤል ያሉ ሰፋፊ እርሻዎች እንዲሁም የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀምና አሠራራቸውን በማዘመን ውጤታማ እየሆኑ የመጡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አርዓያነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ለዋና ዋና ዓለምአቀፍ ገበያዎች በሚያመች የቦታ ርቀት ላይ የምትገኝ ስትሆን የንዑስ ዘርፉን (የሆርቲካልቸርን) ምርት ጥራቱን በጠበቀ ሁኔታ ወደ በርካታ የውጪ መዳረሻዎች የሚያጓጓዝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እጅግ ከዘመነ የማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂና አገልግሎት ጋር ኢንዱስትሪውን በእጅጉ በመደገፍ ላይ ይገኛል። በመንግሥት ልዩ ትኩረትና ድጋፍ አግባብነት ያላቸው የፖሊሲ ማዕቀፎች ተቀርጸው ወደ ተግባር ተገብቷል እንዲሁም ሌሎች በጣም አስቻይና አጋዥ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ለዚህም ባለፈው ዓመት ይፋ ሆኖ ወደ ትግበራ የገባው የአሥር ዓመት ብሔራዊ የሆርቲካልቸር ስትራቴጂ በዋናነት ተጠቃሽ ነው።
እነዚህን የተለዩ እድሎችንና መልካም አጋጣሚዎችን በሚገባ በመጠቀም፤ ከዓለምአቀፍ ተሞክሮች ልምድ በመውሰድና በመማር፤ ለስኬት የሚያበቁ ጅማሮችን በማስፋፋት፥ ለአባል እርሻዎች ለበለጠ ውጤት ሁኔታዎችን ለማሻሻል፥ የዓለምአቀፍ ገበያ እድሎችን ለማስፋት፥ አነስተኛ አርሶአደሮችንና በዘርፉ የተሰማሩ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በሚያስፈልጋቸው በመደገፍ በአጠቃላይ በሀገሪቱ የሙዝ እሴት ሰንሰለት ስኬታማነት የሚታዩ ክፍተቶችን በሚገባ በመሙላት ወደ ላቀ ደረጃ ለመድረስ የሚያስችለውን መንገድ በሚገባ ለማደላደል የኢትዮጵያ አበባ፥ አትክልትና ፍራፍሬ (ሆርቲካልቸር) አምራች ላኪዎች ማኅበር ለሀገሪቱ የሙዝ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ሚና ያላቸውን ቁልፍ ተዋንያንን እና ባለድርሻ አካላትን በአንድ ጣሪያ በማሰባሰብ የሀገሪቱን እምቅ አቅምን በሚገባ በመጠቀምና የሙዝን እሴት በማላቅ ተጠቃሚነትን በእጅጉ ማሳደግ በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ የሚያጠነጥን የአንድ ቀን ጉባዔ “በሙዝ እሴት ወደ ላቀ ስኬት” በሚል መርህ በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል አካሂዷል።
“በሙዝ እሴት ወደ ላቀ ስኬት” ለሚለው መርህ ማን ጋር ምን አለ?
ማኅበሩ ባዘጋጀው ጉባዔ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የተቋማት ተወካዮች፥ የግብርና በተለይ የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያዎች፥ አምራቾች፥ ላኪዎች፥ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፥ የገንዘብ፥ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ኃላፊዎችና ተወካዮች፥ እንዲሁም የልማት አጋሮች፥ ሎጅስቲክስንና ትራንስፖርትን ጨምሮ በሙዝ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ቁልፍ ተዋንያን የሆኑ አካላት ተሳትፈዋል።
እነዚህ ቁልፍ ተዋንያን ዋና ዋና የባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተካሄደው ጉባዔ ላይ በሀገሪቱ የምርቱን ጥራት በማሳደግ፥ በእሴት ሰንሰለቱ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍና በማሻሻል ኢንዱሰትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ ለመውሰድ የሚረዱ የከፍተኛ ባለሙያዎች ጽሑፎች ቀርበዋል፤ በኢንዱሰትሪው መሪዎችና ባለሙያዎች የተናጋሪነት ተሳትፎ ሰፋ ያለ የፓናል ውይይት ተካሂዷል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለምአቀፍ የሙዝ ኢንዱስትሪ ከምርትና ከገበያ አንጻር የተዳሰሰ ሲሆን መጻኤ ሁኔታውንና በዓለምአቀፉ የሙዝ ንግድ በመጪው በምን መልኩ መሳተፍ እንደሚቻል ተጠቁሟል። በሌላ በኩል የግል ኩባንያዎችና አግባብነት ያላቸው ተቋማት ለሙዝ ኢንዱስትሪው ዕድገት እያደረጉ ያሉት አስተዋጽኦ እንዲሁም ተሞክሮአቸውን አጋርተዋል። ለምርቱ ወጪ-ንግድ እጅግ ፋይዳው በጎላው የቀዝቃዛ ሰንሰለት ሎጅስቲክስ እንቅስቃሴ ዙሪያም ጽሑፍ ቀርቧል።
ከመንግስት፥ ከአምራች፥ ከገንዘብ ተቋም፥ ከኅብረት ሥራ ማኅበር፥ ተያያዥነት ካለው ተቋም በመጡ የመድረክ ተሳታፊዎች የተካሄደው የፓናል ውይይት የኢትዮጵያን የሙዝ እሴት እምቅ አቅምን በሚገባ መጠቀም በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ ተከናውኗል። ከጉባዔው ተሳታፊዎች በቀረቡ ጥያቄዎች መሠረት ከመድረኩ በተነሱ ሐሳቦች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል።
ወደ ተፈለገው ስኬት ለመድረስ በሚደረገው ጉዞ ላይ የሚያዘው ስንቅ
የግብርና ሚኒስቴር ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ጉባዔውን በይፋ በከፈቱበት ወቅት ሲናገሩ ከሙዝ ምርት የበለጠ ተጠቃሚነትን ለማሳደግና የላቀ ስኬት ላይ ለመድረስ ከምርት መጠን መጨመር ባለፈ በምርቱ ጥራት ላይ በትኩረት መሠራት እንዳለበት ጠቁመው ለዚህም የባለድርሻ አካላት ርብርብና በቁርጠኝነት የሚደረግ የተጠናከረ ቅንጅት እንደሚገባ አስመረው ተናግረዋል። ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከማኅበሩና ከሌሎች ቁልፍ ተዋንያን እንዲሁም የልማት አጋሮች ጋር በጋራ ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በጉባዔው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አበባ፥ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዴ ኢትዮጵያ በሙዝ እሴት ያላትን እምቅ አቅም በሚገባ በመጠቀም ከኢንዱስተሪው ወጪ ንግድ በመቶ ሚሊዮኖች ከዛም ባለፈ እንደ ላቲን አሜሪካኖቹ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደምትችል ገልጸዋል።
ለዚህም በዋናነት ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የማብቀያና የችግኝ ማዘጋጃ ቴክኖሎጂዎች፥ የአቅም ግንባታ እንዲሁም በእሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚሳተፉ ተዋንያን የተቀናጀ አሠራር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ኢንዱስትሪው በተለይ የገንዘብ አቅርቦት በእጅጉ የሚሻ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህም የገንዘብ ተቋማትን ከፍ ያለ ድጋፍና ጠንካራ ትብብር ጠይቀዋል። ጉባዔው የሆርቲካልቸሩን ንዑስ ዘርፍ በተለይ ሰብል-ተኮር ኢንዱስተሪን ለማጎልበትና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን በእጅጉ ለማሳደግ ማኅበሩ የሚያካሂዳቸው ተከታታይ ሁነቶች አካል መሆኑን የተናገሩት አቶ ቴዎድሮስ በሙዝ እሴት ወደ ላቀ ስኬት የሚለውን መርህ እውን ለማድረግ መሰል ዝግጅቶችና ሰልታዊ ጥረቶች ከቁልፍ ተዋንያን፥ ከባለድርሻ አካላትና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት ጉባዔው ትኩረት በሚሰጥባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር የሀገሪቱን የሙዝ እሴት በማላቅ ከኢንዱስትሪው ተጠቃሚነትን በእጅጉ ለማሳደግ ይረዳሉ ያላቸውን አካሄዶች ጠቁሟል። በዚህም ረገድ የምርት ጥራትን ለማላቅ ሚናቸው የጎላ ቴክኖሎጂዎችና አሠራሮች ላይ ማተኮር፤ ለኢንዱስትሪው ለተሳለጠ የገንዘብ አቅርቦት አገልግሎት የሚረዱ አሠራሮችን መንደፍና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ተቀራርቦ መሥራት፤ ምርትን በተፈለገው መጠንና ጥራት ከማቅረብ ባለፈ የገበያ ልማት ላይ መሥራት፤ ተወዳዳሪነትን መሠረት ያደረገ የገበያ ዋጋ፤ የሎጅስትክስና መሰል ደጋፊ አገልግሎቶችን ማስፋፋት፤ የኢትዮጵያን የሙዝ ምርት ጥራቱንና ተወዳዳሪነቱን የሚያስጠብቅ ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋት፤ በሙዝ እሴት ሰንሰለትና በኢንዱስትሪው ዕድገት ቁልፍ ሚናዎች የሚኖራቸውን አካላት የሚያሰባስብና ለላቀ ስኬት የሚመክር መድረክ መፍጠርና በሀገር ውስጥ በሙዝ ምርት የእሴት ጭማሪ እንቅስቃሴዎችን ማጎልበትና ማስፋፋት የሚሉ ሐሳቦችን ጉባዔው ጠቁሟል።
ጉባዔውን በማዘጋጀቱ ማኅበሩ ከፍተኛ ምስጋና የተቸረው ሲሆን ለታላቁ ጉዞ መሠረት የሚጥል ሁነኛ ጅማሮ እንደሆነ የጉባዔው ተሳታፊዎች ተናግረዋል።





















f